አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሳዑዲ አረቢያ ድሮኖችን ማምከን የሚችሉ ጸረ ድሮኖች ከዩክሬን ለመግዛት ንግግር መጀመሯ ተሰምቷል፡፡
ሀገሪቱን በርካታ ሚሊየን ዶላሮች ሊያስወጣት እንደሚችል የተገለጸው የግዥ ድርድር እስካሁን ስምምነት ላይ አለመደረሱን ዎልስትሬት ጆርናልን ጠቅሶ ሚሊተሪ ኒውስ ዘግቧል።
የዩክሬን ጸረ ድሮኖች በድሮኖች የሚደረገውን ጥቃት ከመነሻቸው ጀምሮ በመከታትል ጥቃት ሳያደርሱ ማክሸፍ የሚችሉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ሳዑዲ ከጸረ ድሮን በተጨማሪ ለስለላ የሚያገለግሉ የኤሌክትሮኒክ ጦርነት ስርዓትን ከዩክሬን ልትገዛ ስለመሆኑም ተገልጿል።
12ኛ ቀኑን በያዘው የአሜሪካ – እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ኢራን በሳዑዲ በፈፀመችው የድሮን ጥቃት በግዙፉ የታኑራ ነዳጅ ማብላያ፣ በሪያድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ሌሎች ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሷ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ የኳታር ተወካዮች ዩክሬን በጦርነቱ ወቅት ድሮኖችን በማምከን ረገድ ያላትን ልምድ ለመቅሰም በኬቭ ጉብኝት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የኢራንን ሻሂድ ድሮኖች ለማምከን ከአሜሪካ፣ አውሮፓ ሕብረት እና መካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ 11 ሀገራት የድሮን ግዥ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ ዩክሬን በጆርዳን የሚገኘውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ለመካለከል የጸረ ድሮን ልዩ ወታደራዊ ልዑክ ወደ ስፍራው መላኩንም ገልጸዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ