የሀገር ውስጥ ዜና

የአየር ኃይሉን ግዙፍ አቅም አቀናጅቶ የሚመራ ብቁ አመራር ማፍራት የተቋሙ የህልውና ጉዳይ ነው – ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

By Mikias Ayele

March 11, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአየር ኃይሉ እየተፈጠረ ያለውን ግዙፍ አቅም አቀናጅቶ የሚመራ ብቁ አመራር ማፍራት የተቋሙ የህልውና ጉዳይ ነው አሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፡፡

ዋና አዛዡ በአየር ኃይል አካዳሚ የአመራር ኮሌጅ ለአምስት ሳምንታት የወታደራዊ አመራርነት ስልጠና ሲወስዱ ለቆዩ ከፍተኛ መኮንኖች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ወታደራዊ መሪ በሥራ ታታሪነት ምሳሌ መሆን፣ የአዕምሮና የሥነ ልቦና ጥንካሬን መላበስ እንዲሁም በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ችግር ፈቺና ታማኝ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ወታደራዊ መሪ ባልተገመቱ ሁኔታዎች ውስጥ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠት የሚችል ነው በማለት ገልጸው÷ መሪዎች ሰራዊቱን ለውጊያ ከማዘጋጀታቸው ባለፈ ሥነ ልቦናዊ እና ቴክኒካዊ ሁኔታዎችን በማጣመር ሰራዊቱን ለተልዕኮ የሚያዘጋጁ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

አየር ኃይሉ በአሁኑ ወቅት ጀግና ተዋጊ ፓይለቶችን፣ ኢንጂነሮችንና ቴክኒሺያኖችን በጥራትና በብቃት እያፈራ ነው ያሉት ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ÷ ይህንን ግዙፍ አቅም አቀናጅቶ የሚመራና የሚያዋጋ ብቃት ያለውን አመራር ማፍራት የተቋሙ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከፍተኛ መኮንኖቹ በዲሲፕሊንና በሁሉም ረገድ ምሳሌ በመሆን ሰራዊቱን ማሰልጠንና ማብቃት እንዳለባቸው አቅጣጫ መስጠታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።