አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለእስልምና እምነት ተከታይ ሰራተኞቹ ባዘጋጀው የአፍጥር መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼኽ አብዱልከሪም ሼኽ በድረዲን ባስተላለፉት መልዕክት÷ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍጥር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት በተለየ ክብር እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።
ሁሉም ዜጋ ለሰላምና ለሀገር ልማት በጋራ ሊሰራ ይገባል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ÷ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ልማት ለማስቀጠል ሁሉም በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸናን (ዶ/ር) ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የእምነቱ ተከታይ የተቋሙ ሰራተኞች መሳተፋቸው ተገልጿል።
በለይኩን ዓለም