አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ወደ ስራ መግባት የፖሊስ ወንጀል ምርመራ፣ ወንጀል መከላከል እና የትራፊክ ስራዎችን አቅልሏል አሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል።
የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአይቲ ባለሙያዎች በተገኙበት የፋይዳ መታወቂያን በተመለከተ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በመድረኩ እንዳሉት፤ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆን የፖሊስ አባላት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
ፋይዳ መታወቂያ ፖሊስ የሚያከናውናቸውን ተግባራትን በማቅለልና በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ወንጀለኞችን በቀላሉ ለመለየት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የፖሊስ ጥቆማ መስጫ መተግበሪያ እና ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የተሳሳረ እንደሆነም አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም ልማዳዊ የነበሩ ስራዎችን በዲጂታል መንገድ እና ስርዓት ለማከናወን መደላድልን እንደፈጠረም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የፋይዳ መታወቂያን ወደ ስራ ማስገባቷ የሰላም እና ጸጥታ ተግባራትን ከማዘመን የተሻገረ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ የፋይዳን ሁለንተናዊ ጥቅም በመገንዘብ የፖሊስ አባላት የፋይዳ መታወቂያ ተደራሽ እንዲሆን መስራት አለባቸው ብለዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት እንዲሆን የፖሊስ አባላት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ማንነትን መካድ እና ማጭበርበር የማይቻልበት ሀገር ለመፍጠር ፖሊስ ለሚያደርገው ሁለንተናዊ ጥረት የፋይዳ መታወቂያ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ በየሳምንቱ 1 ሚሊየን ሰዎች የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ እያደረጉ መሆኑን አንስተው፤ እስካሁን የፋይዳ ተጠቃሚዎች ቁጥር 38 ሚሊየን ደርሷል ብለዋል።
በመራኦል ከድር