አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ‘ፍቼ ጫምባላላ’ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ጃጎ አገኘሁ እንዳሉት ፥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የፊቼ ጫምባላላ በዓል ክልሉ ካሉት የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡
የፍቼ ጫምባላላ በዓል እሴቱን ጠብቆና የቱሪዝም ዘርፉን በሚያነቃቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምኦን በበኩላቸው÷ የበዓሉ ተሳታፊ እንግዶች በቆይታቸው አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
በዓሉ የክልሉን ሕዝብ ትብብርና ሰላም እሴቶች በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲከበር የጸጥታ አካላት ከአስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ፍቼ ጫምበላላ ሰላምን፣ አንድነትንና መከባበርን የያዘ በመሆኑ ሕዝቡ እሴቱን ጠብቆ ሊያከብር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በበዓሉ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡
በዓሉን ለመታደም ሀዋሳ የሚገኙት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት የከተማዋን ኮሪደር እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ በቆይታቸው በቀጣይ ሥራቸው የክልሉን ሕዝብ ባሕል፣ እሴትና ወግ እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ ጉብኝቶችን እንደሚያደርጉ ተመላክቷል፡፡
የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምበላላ በዓል የፊታችን መጋቢት 5 እና 6 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል፡፡
በደብሪቱ በዛብህ