አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በአርባ ምንጭ ከተማና በጋሞ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የኩልፎ ወንዝ ሙላት ያስከተለውን ጉዳት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በጋሞ ዞን በተለያዩ አከባቢዎች በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ እስካሁን የ52 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተመላክቷል፡፡
አፈ ጉባዔ ታገሰ በአርባ ምንጭ ከተማና በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ደጋማ ወረዳዎች በአደጋው የደረሰውን ጉዳት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በአደጋው በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ ድርጅቶች እንዲሁም በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ከባድ የንብረት ውድመት መድረሱና ዜጎች መፈናቀላቸው ተጠቁሟል፡፡
አፈ ጉባዔ ታገሰ በዚህ ወቅት፥ በአካባቢው በተከሰተው የውሃ መጥለቅለቅ እና ናዳ አደጋ በጠፋው የሰው ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ከዞኑ ጋር በመቀናጀት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እያከናወነ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍና የነፍስ አድን ሥራ አድንቀዋል፡፡
አፈ ጉባዔው ዜጎች በኢትዮጵያዊ የመተሳሰብ እና የመደጋገፍ ባሕል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡