ቢዝነስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውጤታማነት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

By Abiy Getahun

March 13, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውጤታማነት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት እና ልማት ወሳኝ ነው አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዚዳንቱ የ12ኛው ጥራት ሽልማት አሸናፊ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአገልግሎቱ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት እየተገበራቸው ያሉ ስራዎችን ተመልክተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውጤታማነት ምንጭ የተቋም ግንባታ ባህሉ ጠንካራ እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ግሩፑ በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተጓዦችን የማስተናገድ አቅሙ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ የካርጎ አገልግሎቱ በዓመት አንድ ሚሊየን ቶን ማስተናገድ የሚችል አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።

ተቋሙ በፈረንጆቹ 2040 የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ቁጥር 242 የማድረስ ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በአሸናፊ ሽብሩ