አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው የመሬት ናዳ እና የጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የ3 ቀናት ብሔራዊ ሀዘን ታውጇል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት፥ በዞኑ ጋጫ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ከጠፉ 125 ሰዎች ውስጥ የ80 ወገኖችን ሕይወት አልፏል።
የቀሪ ሰዎች አስከሬን ፍለጋ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ በዜጎቻችን ላይ በተከሰተው አደጋ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የሰንደቅ አላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ (2) ብሔራዊ የሀዘን ቀንና ሰንደቅ አላማው ዝቅ ብሎ የሚውለበለብባቸውን ሁኔታዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ መደንገጉን ገልጸዋል።
በዚሁ መሠረት በመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸው ያለፈው ዜጎቻችንን በማስመልከት ከመጋቢት 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ታውጇል ብለዋል።
በእነዚህ ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንጽላ ጽ/ቤት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።