አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝነት ያላቸው ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይደረጋሉ፡፡
የሊጉ መሪ አርሰናል በሜዳው ኤቨርተንን የሚያስተናግድ ሲሆን፥ ተከታዩ ማንቼስተር ሲቲ ወደ ለንደን ስታዲየም አቅንቶ በወራጅ ቀጣና የሚገኘውን ዌስትሃም ዩናይትድ ይገጥማል፡፡
መድፈኞቹ ከኤቨርተን ጋር ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሦስቱን ሲያሸንፉ፥ በሁለቱ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ባለፉት የሊጉ ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደው አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር ዛሬ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ከኤቨርተን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያለው ከሊጉ መሪ አርሰናል በሰባት ነጥብ ዝቅ ብሎ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቼስተር ሲቲ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ከሜዳው ውጪ ዌስትሃም ዩናይትድን ይገጥማል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡
ለቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ እየተፎካከረ የሚገኘው ቼልሲ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 በስታምፎርድ ብሪጅ ኒውካስል ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ያለፉት አምስት ግንኙነታቸው በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናቸው፥ ቀሪውን አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡
በርንሌይ ከቦርንማውዝ፣ ሰንደርላንድ ከብራይተን በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት የሚደረጉ የዛሬ መርሐ ግብሮች ናቸው፡፡