ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት…

By Hailemaryam Tegegn

March 14, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካና እስራኤል በአንድ ጎራ እንዲሁም ኢራን በሌላ ወገን ወደ ግጭት የገቡበት ሰሞንኛው የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት 15ኛ ቀኑ ላይ ደርሷል፡፡

በዋናነት ኢራን እና እስራኤልን ጨምሮ በቀጣናው 12 ሀገራት የጥቃት ኢላማ የተደረጉ ሲሆን፥ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡

ከወታደራዊ መሰረተ ልማቶች ባሻገር ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ መስመሮችን ኢላማ ባደረጉ ጥቃቶች በርካታ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሰለባ ሆነዋል፡፡

በእስካሁኑ ሂደት ኢራን በእስራኤል፣ ቆጵሮስ፣ ጆርዳን፣ ኩዌት፣ ኢራቅ፣ ባህሬን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ኦማን እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ፈጽማለች፡፡

በአንጻሩ እስራኤልና አሜሪካ በጋራ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ኢራን፣ ሊባኖስ እና ኢራቅን ኢላማ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡

በአካባቢው የቀጠለውን ውጥረት ተከትሎ በተለይም የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ እየተፈጸሙ የሚገኙ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር አድርጓል፡፡

በዛሬው ዕለት በወጡ ዘገባዎች አሜሪካ የኢራን ወሳኝ የነዳጅ ምርት ማከማቻ በሚገኝበት ካርግ ደሴት ላይ የሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች፡፡

በደሴቲቱ ጥቃት መፈጸሙንና 15 ያህል ጊዜ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን አረጋግጠው በነዳጅ መሰረተ ልማት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸው ጦር ጥቃቱን መፈጸሙን ገልጸው፥ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ካላቆመች የነዳጅ ማከማቻው ቀጣይ የጥቃት ኢላማ ይሆናል ሲሉ ዝተዋል፡፡

በእርግጥ የነዳጅ መሰረተ ልማቱን ኢላማ ያደረገ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ እጥረትና ያለውን የዋጋ ንረት እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ