የሀገር ውስጥ ዜና

በሴትነቴ የሚገጥሙኝ ችግሮች ከዓላማዬ ሳያደናቅፉኝ 3 ነጥብ 98 በማምጣት የማዕረግ ተመራቂ ሆኛለሁ – ሊና ወዩ

By abel neway

March 14, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሴትነቴ የሚገጥሙኝ ችግሮች ከዓላማዬ ሳያደናቅፉኝ የማዕረግ ተመራቂ ሆኛለሁ አለች በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የ18ኛ ዙር የማርኬቲንግ ማኔጅመንት የማዕረግ ተመራቂዋ ሊና ወዩ።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካስመረቃቸው ከ1 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች ውስጥ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ሊና የሜዳሊያ እና የሁለት ዋንጫ ተሸላሚ ሆናለች።

ሊና አማካይ ውጤት 3 ነጥብ 98 በማስመዝገብ ነው የሜዳሊያ እና የሁለት ዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው፡፡

ለዚህ ውጤት የበቃሁት በርትቼ በመስራቴ ነው የምትለው ሊና÷ ሴት መሆን በራሱ ፈታኝ ቢሆንም ፈተናዎችን በማለፍ የገጠሙኝ ችግሮች አጠንክረውኝ ለዚህ በቅቻለሁ ብላለች።

ማንም ሰው ጠንክሮ ከሰራ ካሰበበት ይደርሳል ፤ በተለይ ሴቶች ዓላማ ካላቸውና ግብ ካስቀመጡ ስኬታማ መሆን ይችላሉ ነው ያለችው የማዕረግ ተመራቂዋ፡፡

በታሪኩ ለገሰ