አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትግራይ ክልል ለልማትና ሰላም ግንባታ የተሰለፉ ወጣቶችን ትፈልጋለች አሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)።
በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል በሱዳን የቆዩና የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ከቀድሞ ሕወሃት ጎን የነበሩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ አባላት የተሃድሶ ሥልጠና ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመድረኩ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ተገኝተዋል።
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት የሰላም አማራጭን በመከተል ወደ ሀገራቸው በመመለስ የተሀድሶ ስልጠና በመከታተላቸው አባላቱን አድንቀዋል።
የፌዴራል መንግስት በትግራይ ሰላምን ለማፅናትና ልማትን ለማረጋገጥ ያልሞከረው ሙከራ እንደሌለ ጠቁመው÷ ቆሞ ቀሩ የቀድሞ ሕወሓት ቡድን ከህዝብ በላይ ነኝ በሚል እሳቤ አሁንም እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል።
ቡድኑ በሚያሰራጨው የሐሰት ወሬ ሕዝቡ ሊደናገር አይገባም በማለት ከመንግስት ጎን ሆኖ ልማቱን እንዲያፋጥን ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ቆሞ ቀር ቡድን ሥልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ሀገር ከማልማት ይልቅ የግል ጥቅምን ያስቀደመ እንደነበር አስታውሰዋል።
የፌዴራል መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የሚጠበቅበትን ተግባራት ሁሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ወጣቱ ከግጭት አውድማ ወጥቶ ሰላምን መምረጡ ለራሱም፣ ለክልሉም ሆነ ለሀገሩ ትልቅ ስኬት መሆኑ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ትግራይ ክልል የሚያስፈልጋት ለልማትና ለሰላም ግንባታ የተሰለፈ ወጣት እንጂ ለግጭት የሚማገድ እንዳልሆነም አስገንዝበዋል።
በሀገሪቷ በማንኛውም አካባቢ የመስራትና የመንቀሳቀስ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀድሞ የሕወሓት ቡድን የሚነዙ የተሳሳቱ አሉባልታዎችን ውድቅ አድርገዋል።
ትግራይን ወደ ፊት ማራመድ የሚቻለው በግጭት ሳይሆን ሰላምን መሠረት ባደረገ ኃይል ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው÷ እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተሳተፉና በሱዳን ድንበር አካባቢ የነበሩ ናቸው ብለዋል።
የሰላምን አማራጭ በመቀበል ወደ ማዕከሉ የመጡትን ዜጎች የመለየት፣ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥራ በጥንቃቄ ተከናውኖ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና እንዲገቡ ተደርገዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡