አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ በዓል ዛሬ በሶሬሳ ጉዱማሌ እየተከበረ ነው።
በዓሉን አስመልክቶ ትናንት በባህል አደራሽ የፊጦራ ሥነ ሥርዓት የተደረገ ሲሆን፥ ሥርዓቱ አሮጌውን ዓመት የመሸኘትና ፆም የመፍታት ሥርዓት እንዲሁም ያለፈው ዓመት የሰራነውን ሐጢያት ይቅር በለን ተብሎ የተጣላ ታርቆ ማዕድ በጋራ ተቆርሶ ወደ ዛሬ ቀን ሽግግር የሚደረግበት ነው።
ዛሬ ደግሞ ”በሶሬሳ ጉዱማሌ” አዲሱ ዓመት ወይም ”ፍቼ ጫምባላላ” ከማለዳ ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
በፍቼ ጫምባላላ አከባበር ላይ የሚከወነው ዋነኛው ጉዳይ የአባቶች ቄጣላ ሲሆን፥ በዓመት አንድ ጊዜ የሲዳማ ብሔር የፍቼ ጫምባላላ አውዶችን ተንተርሶ የሚከናወን ሥርዓት ነው፡፡
ክብረ በዓሉ በስልታዊ የአካል እንቅስቃሴ ታጅቦ በጥዑም ዜማ ምስጋና የሚቀርብበትና መልዕክት የሚተላለፍበት የማራኪ ትዕይንት መድረክ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ወንዶች ”ጎንፋ” የተባለ በህላዊ ልብስ የሚለብሱ ሲሆን፥ የሴቶች ደግሞ ”ቆንጦሎና ቆሎ” የተባሉ ባህላዊ ልብሶችን ለብሰው በዓሉን እየታደሙ ናቸው።
በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
በጥላሁን ይልማ