አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሃይማኖት ተቋማት በከተማዋ ሁለንተናዊ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ላይ የማይተካ አስተዋጽኦ አላቸው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በክፍለ ከተሞች ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ማጠቃለያ ተካሂዷል።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በከተማችን ከሚገኙ የእስልምና እምነት አባቶች እና ምእመናን ጋር ዛሬ ማለዳ ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃ ሃይማኖት፣ ባህል እና ትውፊት ባለቤት የሆነች ሀገር ናት ያሉት ከንቲባዋ፥ አንዱ ደምቆ ሌላው ደብዝዞ የሚታይባት ሳትሆን ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚደምቁባት ናት ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ መንግሥትም ሁሉንም ሃይማኖቶች በእኩልነት እንመለከታለን፤ በእኩልነት እናገለግላለን በማለት አመልክተዋል።
እንደ ሌሎቹ ሀይማኖቶች ሁሉ፤ እስልምና የኢትዮጵያን ጥንታዊ ቅርሶች፣ ታሪኮችና ትውፊቶች ጠብቆ ለትውልድ በማሸጋገር፣ ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ፣ ግብረ-ገብነትንና ሰብአዊ ርህራሄን በማስተማር ሚና እንዳለው አንስተዋል።
እስልምና በልማት ተሳትፎው የዛሬዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ረገድ ያለው ሚና የጎላ ነው ብለዋል።
በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሃይማኖት ተቋማት በከተማዋ ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ላይ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑንም አስረድተዋል።
በውይይታችንም ይህንን ጉልህ ሚና ይበልጥ በማጠናከር እጅ ለእጅ ተያይዘን ለልማት፣ ለህዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለሰላም እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ የምንቆምበት እና በጋራ የምንሰራበት አግባብ ላይ ተግባብተናል ነው ያሉት።
ውይይቱ በሂደት የታዩ ክፍተቶችን ማረም በሚቻልበት አግባብ ላይ በመወያየት በትብብር ለማረም የሚስችል መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክ ነበር ብለዋል።
የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ እንዲሁም የጋራ መግባባት የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።
የእስልምና እምነት አባቶች እና ምዕመናን ለነበራቸው ከፍተኛ ተሳትፎ፣ ለሰጡት ገንቢ ሐሳብና አስተያየት ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።