የሀገር ውስጥ ዜና

የጋዜጠኛ ታሪኩ ኦላና ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ

By Mikias Ayele

March 15, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀድሞ ፋና ሬዲዮ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጠኛ የነበረው ታሪኩ ኦላና ሥርዓተ ቀብር በቀጨኔ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና የቀድሞ የስራ ባልደረቦቹ ተገኝተዋል።

ባጋጠመው ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ሌሊት በተወለደ በ61 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ጋዜጠኛ ታሪኩ ኦላና፤ በ1957 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ ነው የተወለደው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ትምህርቱን እንደጨረሰ የቀድሞውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (የአሁኑ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሸን) በመቀላቀል በአፋን ኦሮሞ ክፍል በሚዲያው ዘርፍ የኦሮሞን ሕዝብ ባሕልና ቋንቋ በማሳደግ ረገድ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

በዚህም በአድማጭ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበረው።

ጋዜጠኛ ታሪኩ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበር።

በፌናን ንጉሴ