ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፈተች

By Mikias Ayele

March 15, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተካሄደ ባለው ጦርነት እስራኤል በምዕራባዊ ኢራን መጠነ ሰፊ ጥቃት መክፈቷ ተሰምቷል፡፡

የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው፤ ዘመቻው በምዕራባዊ ኢራን የሚገኙ የአብዮታዊ ዘቡ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረገ ነው።

በተመሳሳይ ኢራን በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል እንዲሁም በኢራቅ እና በኩዌት ወደሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በማስወንጨፍ ጥቃት ፈፅማለች መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ኢራን ከትናንት ጀምሮ የአሜሪካ እና እስራኤል አጋር ባለቻቸው ሀገራት ላይ ጥቃት እየፈፀመች ሲሆን፤ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ በአምስት የቀጣናው ሀገራት ላይ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች ሰንዝራለች፡፡

ኢራን ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን ያረጋገጠው የእስራኤል መከላከያ ሀይል፤ በጥቃቱ ሁለት ሰዎች ተጎድተዋል ብሏል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን መደራደር ትፈልጋለች ነገር ግን የሚያስማማ የድርድር ሃሳብ የላትም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሆርሙዝ ሰርጥን ለማስከፈት ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት የባሕር ሀይላቸውን ወደ አካባቢው በማስጠጋት የአሜሪካን ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

በሚኪያስ አየለ