አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአራትዮሽ ዋንጫ እየተፎካከረ የሚገኘው ማንቼስተር ሲቲ በቀጣይ በተለያዩ ውድድሮች በሚያደርጋቸው አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የማንቼስተር ሲቲ ቀጣይ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች የቡድኑ የዋንጫ ጉዞ ላይ የሚወስኑ ሲሆን ከአምስቱ ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ከአርሰናል ጋር ይገናኛል፡፡
በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ ነገ ምሽት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ የ15 ጊዜ አሸናፊ ከሆነው ከስፔኑ ቡድን ሪያል ማድሪድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ከባዱን የተከታታይ መርሐ ግብር ፈተና ይጀምራል።
ማንቼስተር ሲቲ ወደ ስፔን አቅንቶ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በሪያል ማድሪድ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ በመመለሱ ውጤቱን በሜዳው ኢትሃድ በሚያደርገው ጨዋታ ቀልብሶ ለማለፍ ከሪያል ማድሪድ ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ውጤቱን ቀልብሶ ሩብ ፍጻሜውን የመቀላቀል ዕድሉ በኦፕታ ቅድመ ትንበያ መሰረት 17 ነጥብ 1 በመቶ ነው፡፡
ከዚህ ከባድ ፍልሚያ በኋላ ማንቼስተር ሲቲ የፊታችን እሁድ በካራቦ ካፕ ፍጻሜ ከአርሰናል ጋር ይፋለማል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት የአራትዮሽ ዋንጫ ለማሳካት እየተፋለሙ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ዋንጫ ለማንሳት የሚደያርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
ማንቼስተር ሲቲ 9ኛ የካራቦ ካፕ እና የዚህን የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዋንጫውን ለማሳካት በሚያደርገው ጉዞ ከአርሰናል ከባድ ፉክክር የሚጠብቀው ይሆናል፡፡
ሲቲ ከዌይምብሌ ስታዲየም የካራቦ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ በኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ከመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ሌላኛው ከባድ ፈተና ተደቅኖበታል።
ማንቼስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ጋር በዚህ የውድድር ዘመን በሊጉ ያደረጋቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ከሊቨርፑል የኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ በመቀጠል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከቼልሲ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
የአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት እና ከሊጉ መሪ አርሰናል ላለመራቅ የሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ ነው፡፡
ተጋጣሚው ቼልሲ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት የሚያደርገው ጨዋታ በመሆኑ ማንቼስተር ሲቲ በጨዋታው ከባድ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ከስታምፎርድ ብሪጅ ወሳኝ ጨዋታ መልስ በሜዳው ኢትሃድ በ33ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ይገናኛል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዘመን በሊጉ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የኢምሬትስ ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
በሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚደያርጉት የ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ትልቅ የውጤት ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ