የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ሥራዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት 61ኛው የቬኒስ ቢየናሌ…

By Yonas Getnet

March 16, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጣሊያን ቬኒስ ከተማ በሚካሄው 61ኛው የቬኒስ ቢየናሌ ላይ “የዝምታ ቅርጾች” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ዓውደ ርዕይ ለዕይታ ታቀርባለች፡፡

በሰዓሊ ተገኔ ቁንቢ አማካይነት በሚቀርበው የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን “የዝምታ ቅርጾች” የተሰኘ ዓውደ ርዕይ ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

ዓውደ ርዕዩ በዓለም አቀፍ የሥዕል ሥራዎች ውድድር ያለፉ አርቲስቶች ቀርበው የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡበትና የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ ስለሺ ግርማ ÷ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም እንድታሳይ እድል ይፈጥርላታል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብትና ቅርስ ለዓለም ለማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት በርካታ ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

ዘርፉን ለማልማት በተከናወነው ዘርፈ ብዙ ሥራም ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ መቻሉን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ቱሪዝም ሚኒስቴር ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን እና ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ÷ ለአብነትም አዲሱን የቱሪዝም ፖሊሲ ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ኢኮ ቱሪዝም፣ ጂኦ ቱሪዝም፣ የቡና ቱሪዝም እና የጥበብ ቱሪዝም የሚሉ ዘርፎችን እንዳካተተ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በበኩላቸው÷ዓውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን አመለካከትና የፈጠራ አቅም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኪነ ጥበብ ዘርፍ ለሚገኙ ባለተሰጥኦዎች መነሳሳትን ከመፍጠር አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

“ዝምታ” የኢትዮጵያን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የታጠረ ሐይል አድርጎ የሚያቀርብ ነው ያሉት ደግሞ ሰዓሊ ተገኔ ቁንቢ ናቸው፡፡

በሔብሮን ዋልታው