አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የአካባቢ ጥበቃን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በኩል ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርዓያነት የሚወስዱት ነው አሉ የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን አባላት ሀገራት ተወካዮች።
ተወካዮቹ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማትን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን÷ የመዲናዋን የወንዝ ዳርቻዎችን በማልማት ወደ ሕዝብ መዝናኛነትና የከተማ ውበት አካል እንዲሆኑ የተደረጉበትን ሁኔታ አድንቀዋል።
የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ፌሊክስ ሞሲ ንጋምላጎሲ እንዳሉት ፥ የአፍሪካ ከተሞች የታቀዱ፣ ሳቢ እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ በማድረግ በኩል አዲስ አበባ በአርዓያነት የምትጥቀስ ናት።
በተለይም አሁን ላይ በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉ ለውጦች ከተማዋን ለመዝናኛና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተመራጭ እያደረጓት መሆኑን እና ሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም ትምህርት እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚምባብዌ የመጣጡት ቺቶ ፊሪ በበኩሏቸው የአዲስ አበባ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች በስፋት በመገንባት እየተሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ እንደሆነ ገልጸው÷ ይህም ለከተማዋ ድምቀት በመሆን ለነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች ምቹ ከባቢን ይፈጥራል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ለእግረኛ መንገድ የተሰጠው ትኩረት ለጤና እጅግ ተስማሚ የሆነውን የእግር ጉዞ ባህል ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
ከ15 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር እና አሁን ላይ አዲስ አበባ አስድናቂ ለውጥና ዕድገት ማስመዝገቧን መመልከታቸውን የተናገሩት ደግሞ ከሞዛቢክ የመጡት ማኑኤል ቻጉሎ ናቸው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ልምድ የሚቀሰምበት ተጨባጭ ለውጥ አምጥታለች ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡