የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በጋሞ ዞን በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

By Yonas Getnet

March 16, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክት ÷ለኢፌዲሪ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል፡፡

በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናት በመመኘት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በፍጥነት እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ለነፍስ አድን ሥራ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ያለ እረፍት እየሰሩ የሚገኙ አካላትን አድንቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆም ማረጋገጣቸውን የህብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ለተጎጂዎች እየተከናወኑ በሚገኙ የእርዳታና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡

በጋሞ ዞን የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍና የመሬት ናዳ እስከ ትናንት ድረስ የ81 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡