አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የድንች ምርት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም አለው አሉ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)።
ኢንስቲትዩቱ ከአይሪሽ ድንች ምርምር እና ልማት ማህበር ጋር በመተባበር “የኢትዮጵያ የድንች ኢንዱስትሪን ማሳደግ ለማይበገር የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ እድገት” በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የድንች ምርምርና ልማት ዐውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የድንች ምርት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በትብብር ሊሰራ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ የድንች ምርትን ለውጪ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳላት ገልጸው÷ አሁንም ለተለያዩ ሀገራት ገበያ በማቅረብ ላይ መሆኗን አንስተዋል።
የምርት እሴት ሰንሰለትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው÷ በዚህም ድንች አምራቾችን ተጠቃሚ በማድረግ የገጠር አካባቢ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
ጠንካራ የገበያ ትስስር፣ ምርምር፣ ፈጠራ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዐውደ ጥናቱ ላይ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዮናስ ጌትነት