ቢዝነስ

ስሪላንካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው

By Adimasu Aragawu

March 17, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ እስያዊቷ ሀገር ስሪላንካ በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋም የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አኑራ ኩማራ ዲሳናያኬ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ ለመጥፎ ቀናቶች ዝግጅት እናደርጋለን፤ መልካም ነገር እንዲመጣም ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ የስራ ቀን ውስጥ አንዱን በመዝጋት ብሔራዊ በዓል እንዲሆን በመወሰንና ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ምን ያህል ነዳጅ መግዛት እንደሚችሉ የሚወስን ካርድ በማዘጋጀት እንዲይዙ ማድረጓ ተገልጿል።

ስሪላንካ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ ሌሎች የእስያ ሀገራት የቁጠባ ውሳኔዎችን ካሳለፉ በኋላ ይህንን ውሳኔ ማሳለፏም ተመላክቷል።

በተመሳሳይ ማይናማር፣ ታይላንድ፣ ባንግላዴሽ፣ ፊሊፒንስ እና ቬይትናም የመሳሰሉ ሌሎች የእስያ ሀገራትም በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር በመስጋት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያም በትራንፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በኩል ባወጣችው መግለጫ ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋምና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመታደግ በነዳጅና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በመተው የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

በነዳጅ የሚሰሩትን ወደ ኤሌክትሪክና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ስራን ማጠናከር እንደሚገባም በመግለጽ÷ እስከ 20 ቶን የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ከ20 ቶን በላይ የሚጭኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝና ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በሚኪያስ አየለ