ቢዝነስ

የእንዶዴ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በሎጂስቲክስ ዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Hailemaryam Tegegn

March 17, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንዶዴ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም በማሳደግ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን የጎበኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ፕሮጀክቱ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማሕበር በሎጂስቲክስ ዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እያደረገባቸው ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወነው የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሦስት ወራት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት አፈጻጸሙ 98 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 1 ሺህ ኮንቴነሮች ብቻ የማስተናገድ አቅሙን ወደ 4 ሺህ 500 ከፍ በማድረግ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡

የወደቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የወጪና ገቢ የኮንቴነር ጭነት ማውረድና መጫን ላይ ይወስድ የነበረውን ከ10 ሰዓት በላይ ጊዜ ወደ ሁለት ሰዓት ዝቅ የማድረግ አቅም እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

በምዕራፍ ሁለት የሚከናወነው ፕሮጀክቱ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ብትን ጭነቶች የሚስተናገዱበት የጭነት ማዕከል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር እንደሚፈጅና አሁን ላይ አፈፃፀሙ 22 በመቶ እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በ560 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባ የባቡር ሃዲድ መስመር በእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ውስጥ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በእንዶዴ የጭነት ማዕከል በ1 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘውን አጠቃላይ መጋዘን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መተቀዱን ገልጸው፥ የሎጂስቲክስ ዘርፉን ገቢና ወጪ ምርቶች በማከማቸት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

በሁለት ምዕራፍ እየተከናወነ የሚገኘው የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በዋናነት የሀገሪቱን ብትን ጭነት እንዲሁም መለስተኛና ከፍተኛ ተሽከርካሪዎቸን የማስተናገድ አቅም በአራት እጥፍ የማሳደግ አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ጭነት የማውረድና የመጫን አቅምን በሰባት እጥፍ እንዲሁም የኮንቴነር ማከማቻ አቅምን በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድግ ነው የገለጹት፡፡

በጉብኝቱ የተካተተው የኤ ኤም ጂ- እንዶዴ ባቡር ጣቢያ አገናኝ የሦስት ኪሎ ሜትር የባቡር መሥመር በሀገር በቀል የግል ኩባንያ ፋይናንስ የተደረገ የመጀመሪያው የባቡር መሠረተ ልማት ነው ብለዋል፡፡

ይህም የግል ዘርፉ ለሀገር ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፥ የባቡር መሥመሩ ቡና እንዲሁም በገላን ኢንዱስትሪ ዞን የሚመረቱ ምርቶችን በፍጥነትና በተወዳዳሪ ዋጋ ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ያስችላል ነው ያሉት።

በለይኩን ዓለም