አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮሪደር ልማት የተገነቡ 315 የንግድ ሱቆችን በቀበሌና በንግድ ቤቶች በኪራይ ሲሰሩ ለነበሩ የኮሪደር ልማት ተነሺዎች አስተላልፈናል አሉ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፥ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የተገነቡት የንግድ ሱቆች በዛሬው ዕለት ለልማት ተነሺዎች በዕጣ ተላልፈዋል፡፡
በመዲናዋ ከዚህ ቀደም የመንግስት የቀበሌና የንግድ ቤቶችን ተከራይተው ሲሰሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ሁለት አማራጮችን አቅርቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በአክሲዮን ተደራጅተው ወደ ንግድ ሱቃቸው ገብተው እንዲሰሩ ወይም መንግስት የሚያቀርብላቸውን ሱቆች ተከራይተው እንዲሰሩ አማራጮች ተሰጥቷቸው ነበር ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ መንግስት ገንብቶ ያቀረብላቸውን ሱቆች ተከራይተው ንግዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በአክሲዮን ተደራጅተው በንግድ ሱቃቸው ለመነገድ መምረጣቸውን ገልጸዋል፡፡
በአክሲዮን እንዲደራጁና መሬት ተረክበው እንዲገነቡ ከተፈቀደላቸው ውስጥ የመገንባት አቅም በማጣታቸው በተለያዩ የውይይት መድረኮች ሌላ አማራጭ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ በኮሪደር፣ በወንዝ ዳርቻ ልማትና በመልሶ ማልማት ሥራዎች ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ 315 ዘመናዊ የንግድ ሱቆችን በዕጣ እንዲተላለፉላቸው አድርጓል ብለዋል።