የሀገር ውስጥ ዜና

4 ነጥብ 48 ኪሎ ግራም ኮኬይን በቁጥጥር ስር ዋለ

By Hailemaryam Tegegn

March 17, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሊተላለፍ የነበረ 4 ነጥብ 48 ኪሎ ግራም ኮኬይን በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

መነሻውን ናይጄሪያ ሌጎስ መዳረሻውን ህንድ ባደረገ ተጠርጣሪ ሻንጣ ውስጥ ተደብቆ ሊያልፍ እንደነበር የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ የአቪዬሽን ደህንነት ሰራተኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ አማካኝነት በቁጥጥር ስር ውሏል።

አደገኛ ዕጹ 172 ፍሬ ብዛት ያለው ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በተገጠመ ዘመናዊ ኤክስሬይ መሣሪያ መለየቱ ተገልጿል፡፡

ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ተጠርጣሪና ሌሎች መረጃዎች ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መተላለፋቸውንም ጠቁሟል።