ቢዝነስ

የነዳጅ ብክነት እንዳይኖር ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት – የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን

By Yonas Getnet

March 18, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የነዳጅ ምርት ብክነት እንዳይኖር ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት አሉ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)።

ዳይሬክተሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ መንግሥት የነዳጅ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ በልዩ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል።

የተፈጠረውን ችግር መሰረት በማድረግ ከሁሉም ክልሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከጸጥታ አካላት ጋር በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊደረጉ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እና የቁጥጥር ርምጃዎች የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

በክልሎች በተለይ በማደያ ደረጃ የሚደረጉ የክትትል ስራዎች መጠናከራቸውን ገልጸው÷ እያንዳንዱ ማደያ የቀረበላቸውን ነዳጅ በተቀመጠው የግብይት ስርዓት ብቻ ግብይት እንዲፈጽሙና ለሕዝብ ማመላሻ ተሽከሪካሪዎች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያሰራጩ አሳስበዋል።

ከመደበኛው የነዳጅ መያዣ ታንከር ውጭ ተጨማሪ በማሰራት ነዳጅ ያለግባብ እንዲባክን በሚያደርጉ አካላትና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን መከላከል ላይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል።

በሁሉም ክልሎች በተደረገ ቁጥጥር በሕገወጥ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውን ጠቁመው÷ እስካሁን ድረስ የአቅርቦት ችግር አለማጋጠሙን አስረድተዋል።

የዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓቱ ወደተረጋጋ ሁኔታ እስኪመጣ ድረስ የሕብረተሰቡን የመግዛት አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ እንደሆነና ለናፍጣ በሊትር እስከ 98 ብር እንዲሁም ለቤንዚን እስከ 73 ብር ድረስ እንደሚደጎም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ አጋጣሚውን በመጠቀም በሕገወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ በሚሰማሩ አካላት መንግሥት ርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝና ማሕበረሰቡም እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን ሲመለከት ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እስኪቀረፍ የነዳጅ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከመንግሥት በኩል የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በአግባቡ መተግበር እንደሚያስፈልግ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በመሳፍንት እያዩ