የሀገር ውስጥ ዜና

የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ የሀገር ውስጥ አልሚዎችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል – ኮርፖሬሽኑ

By Yonas Getnet

March 18, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው አዋጅ የሀገር ውስጥ አልሚዎችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል አለ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን።

የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር ያለመ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የፋይናንስ አቅርቦትን በማጠናከር የሀገር ውስጥ አልሚዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ አዋጁ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተሰማሩ ኩባንያዎች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሀገር ውስጥ አልሚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ባሻገር የፋይናንስ አቅርቦትና ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፋይናንስ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዚህም የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅደው አዋጅ ወደ ትግበራ መግባቱ በተለይም የሀገር ውስጥ አልሚዎችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል ነው ያሉት።

ባንኮች በመመሪያው የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልተው በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ አገልግሎት መስጠትና ፋይናንስ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በኃይለማሪያም ተገኝ