ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ እና ብሪታኒያ ችግራቸውን ይፍቱ – ፕሬዚዳንት ቭሎዶሚር ዘለንስኪ

By Adimasu Aragawu

March 18, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከብሪታኒያ ጋር ያላቸውን አለመግባባት እንዲፈቱ ጠየቁ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ብሪታኒያ በኢራኑ ጦርነት ድጋፍ አላደረገችም በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ላይ ተደጋጋሚ ትችት ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ፕሬዚዳንቱ ይህንን ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ሁለቱ መሪዎች በጦርነቱ ያላቸውን አቋም በተለያዩ ጊዜያት እየገለጹ መሆናቸውንና አለመግባባታቸውም እየተካረረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ትራምፕ የሆርሙዝ ሰርጥን ለማስከፈት ብሪታኒያ የባሕር ኃይል ድጋፍ እንድታደርግ ብጠይቁም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ለትራምፕ ጥሪ ጆሮ ዳባ ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እየተካሄደ ባለው ጦርነት አሜሪካን ለመርዳት የዩክሬን ወታደራዊ ልዑክ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መሰማራቱን ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል፡፡

19ኛ ቀኑን የያዘው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በሀገራቸው እና በዓለም ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰው÷ በጦርነቱ ምክንያት ከሩሲያ እያደረጉት ያለው ድርድር ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር መደረጉን አመልክተዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ