የሀገር ውስጥ ዜና

በጋሞ ዞን በተከሰተው አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

By Melaku Gedif

March 18, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል አለ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ፡፡

በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በክልሉ ከሚገኙ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተጎጂዎች መልሶ ማቋቋም ሒደት ዙሪያ መክረዋል፡፡

አቶ ተፈሪ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በጋሞ ዞን በተከሰተው አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የግል ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡

ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት ለተጎጂዎች በገንዘብና በአይነት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ካደረጉ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የወላይታ ዞንና የወላይታ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም፣ የዲላ ክላስተር የክልል ተቋማትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገኙበታል፡፡

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ አናያር ትሬዲንግ ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ኦርቢ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እና ሌሎች ድርጅቶችም ለተጎጂዎች በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በመለሰ ታደለ