የሀገር ውስጥ ዜና

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

By Hailemaryam Tegegn

March 19, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ ዒድ አል ፈጥር በመተባበር የደስታ ብርሃን የሚንፀባረቅበትና ሕይወት በበጎነት የምትደምቅበት ታላቅ ዕለት ነው ብለዋል።

የረመዳን ወር ከእምነቱ በተሻገረ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን በተግባር ያሳየ እንደነበር አስታውሰው፥ ጾሙ አስተሳስቦናል፥ ሶላቱ አቀራርቦናል፥ ኢፍጣሩ በአንድ ማዕድ ዙሪያ ሲያሰባስበን ከርሟል ነው ያሉት፡፡

ለሰው ልጆች ሁሉ ጠቃሚ የሆኑት የዒድ አል ፈጥር ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው፥ በታላቁ የጾም ወቅት የተጀመረውን ኅብረትና መተዛዘን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ሀገር ያለ አብሮነትና በጎነት ስለማይገነባ ለበጎነት መበርታት እንደሚገባ ጠቁመው፥ የበጎነት እጆች ችግርን ወደ ተስፋ፥ እንባን ወደ ሳቅ እንደሚቀይሩ አስረድተዋል፡፡

ኅብረ ብሔራዊ ለሆነችው ኢትዮጵያ መቻቻልና በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት ጌጥ አድርጎ በዓለም ሁሉ ፊት መድመቅ ለነገይቱ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋን የሚሰንቅ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ዘላቂና ዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሁላችንም ለሀገራችን የምንችለውን እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡