አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምንገነባው ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት የሚወሰነው በቅድመ ምርጫ ተሳትፏችን ልክ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ በመጪው ግንቦት የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣይ ብሩህ ዘመኗ የምትሸጋገርበት መሆኑን ገልጸዋል።
ምርጫው ሀገራችን የዴሞክራሲ ድል የምትቀዳጅበት፤ ወደ ቀጣይ ብሩህ ዘመኗ የምትሸጋገርበት በር ነው በማለት ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ለዓመታት ዴሞክራሲን ስንናፍቅ ኖረናል፤ ጉዟችን አልጋ በአልጋ አልነበረም ብለዋል።
ከፈተና በኋላ በረከት፣ ከብርታት በኋላ ሐሴት እንዳለ ከረመዳን ጾምና ከዒድ አል ፈጥር በዓል እንማራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊ ጉዳዮች ውስጥ ዘርና ምርት የተቆራኙ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የምንገነባው ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት የሚወሰነው በቅድመ ምርጫ ተሳትፏችን ልክ ነው በማለት ገልጸው፤ ተሳትፏችን ከጠየመ ዴሞክራሲያችንም ይጠይማል ነው ያሉት።
በደካማ ተሳትፎ ጠንካራ ዴሞክራሲ ማዋለድ እንደማይቻል ገልጸው፤ ዜጎች በምርጫው ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በባዶ መሬት እንደማይበቅል እና በግጭትና ሥርዓት አልበኝነት እንደማይገነባ ጠቅሰው፤ ስክነትን፣ ለትብብርና ቅንጅት ልብን ክፍት ማድረግን፣ በጨዋታው ሕግ መመራትን ይጠይቃል ብለዋል በመልዕክታቸው።