መንደርደሪያ
በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሙስሊሞች የዒድ አል-ፈጥር በዓል አከባበር ትዝታዎች ይኖሯቸዋል። በዓሉ በሁሉም ሙስሊም ልብ ደስታን የሚያጎናፅፉ ወዲህም ከሐይማኖታዊና ባህላዊ ተግባራት ጋር ተጣጥመው የተላለፉ ጥንታዊ ወጎችና ልማዶችም አሉት።
የዒድ አል-ፈጥር በዓልን መምጣት ተከትሎ በተለይም በዋዜማው ወይም ከዚያም በፊት ባሉት የጾም ቀናቶች የሚደረጉ ዝግጅቶች ልዩ ጣዕምና አይረሴነት አላቸው።
ድሮ ድሮ በዓላት ሲከሰቱ የነበሩ የቆዩ እሴቶችና ልማዶች አሁን አሁን ላይ ሳይከለሉ ወይም ሳይሳሱ በፊት ለበዓላት ይሰጡ የነበሩት ዝግጅቶችና ድምቀቶች ሁሌ አዲስ የመሆናቸው ምስጢር አስደናቂ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በያለንበት ቦታና ሀገር ሁሌም በዓላት በመጡ ቁጥር ወደኋላ በሀሳብና በትዝታ የምንነጉደውና ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ለነገ የምንናፍቀው፡፡ በእርግጥ በዓልን በዓል የምናስመስለው እኛው ነን፡፡
ዒድ አል-ፈጥር
የዒድ አል-ፈጥር በዓል ታላቁ የረመዳን ወር ፆም መጠናቀቅን ተከትሎ የሚመጣ ታላቅ በዓል እንደመሆኑ መጠን አማኞቹም በታላቅ አክብሮትና ደስታ ተቀብለው ያስተናግዱታል፡፡ በዕለቱ ሁሉም አማኝ ዘና ፈታ ብሎ እንዲውልና በዓሉን ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት እና ከዘመድ አዝማድ ጋር በደስታ እንዲያሳልፍ ኃይማኖታዊ ህግጋቱ ያዙታል፡፡
የመደጋገፉ ባህሉም በዕለቱ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን ዘካተል ፊጥር ከሚሰጣቸው ጥቅሞች አንዱ በገቢ ዝቅተኛ የሆነው ማህበረሰብም በበዓሉ ቀን አብሮ እኩል የደስታው ተካፋይ እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ነው፡፡
እኔና ዒድ አል-ፈጥር
የዒድ አል-ፈጥር በዓል አከባበር በሀገራችን በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ሲሆን ሐይማኖታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ይከናወናል፡፡ እንደ ማሳያ ተወልጄ ባደኩባት አዲስ አበባ መሐል ፒያሳ በተለይም የጥንቷ ውቤ በረሃ ማንኛውም ሐይማኖታዊም ሆነ ብሔራዊ በዓላት ጎልቶ እና ደምቆ የሚታይበት አካባቢ ነው፡፡
በዚሁ መንገድ ተመሳሳይ ወደ ሆነው የአብዛኛዎቻችን የልጅነት የበዓላት ትዘታዎች አብረን አንዝለቅና ከላይ የጠቀስኳትን ውቤ በረሃ መነሻ አድርጌ በደጃች ውቤ እና ፒያሳ የዒድ አል-ፈጥር በዓል አከባበር ውሏችንን እናስታውስ፡፡
ሙሉ የረመዳንን ወር ፆም ስንፆም አዘውትረን ሶላት በተለይም የተራዊህ ሶላት የምንሰግደው ከድሮው አትክልት ተራ ዝቅ ብሎ ከዋናው ሸዋ ሱፐር ማርኬት ጎን በሚገኘው ጥንታዊው ኑር መስጂድ ነበር፡፡ በየዕለቱ ቤት ባፈራው የማፍጠሪያ ስርዓት ላይ የነበረው ድባብ ራሱ በዓል ይመስል ነበር፡፡ በሌሎች መድረኮችና አጋጣሚዎች ላይ እንደሚነሳው እኛ ቤትም ከጎረቤቶቻችን ጋር የነበረን የአብሮነት ተምሳሌት በየቀኑ ኖረን ያሳለፍነው በመሆኑ አይረሳም፡፡
የተወለድኩበት የደጃች ውቤ ሰፈር በተለይ የኛ ግቢ የራስ ቢትወደድ መኖሪያ ስለነበር ከጊዜ በኋላ በቀበሌ አስተዳደር ስር ተሸንሽኖ እኛን ጨምሮ ወደ ስምንት ቤተሰቦች ይኖሩበት ነበር፡፡ በግቢው ውስጥ ሙስሊም ቤተሰብ የእኛ ቤተሰብ ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የነበረው አብሮነትና ፍቅር እንደ አንድ ቤተሰብ ነበር፡፡
እናም ወደ አፍጥር ስርዓቱ ስመልሳችሁ መቼም የነበረውን ድባብ ቀደም ብዬ ካነሳሁት ሀሳብ የአኗኗር ዘይቤ አንፃር መገመት አይከብዳችሁም፡፡ ምክንያቱም ሁላችሁም በየአካባቢያችሁ የምታውቁት ነውና፡፡ በተለይም የታላቅ እህታችን የክርስትና እምነት ተከታይ ጓደኞቿ የነበራቸው የየዕለት ተሳትፎ ልዩ ድምቀት ነበረው፡፡
ከአፍጥር ስርዓቱ መጠናቀቅ በኋላ ከአባቶቻችን እና ከጓደኞቻችን ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ምግብ አዳራሽ መንገድን ይዘን በእሳት አደጋ መከላከያና በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መካከል ባለችው አስፋልት በማዘጋጃ በኩል በሸዋ ዳቦ ቤት ቁልቁል በመውረድ በታላቁ ኑር መስጂድ የዒሻ እና ተራዊህ ሶላታችን ሰግደን እንመለስ ነበር፡፡
ለረጅም ጊዜ በኑር መስጂድ ላሳለፍን ሙስሊሞች በተለይ ሁለቱ መንታ የመናዊያን ማዲሆች በተራዊህ ሶላት መካከል ያቀርቡት የነበረው ዚክር ከማናችንም ልብ የሚፋቅ ወይም የሚረሳ አይደለም፡፡ የመስጂዱ ግርማ ሞገስ የነበሩት የሀጂ ዑመር ኢድሪስ አስተምህሮትም ፈፅሞ የሚረሳ አይደለም፡፡ ሶላተ-ተራዊህም ከተጠናቀቀ በኋላ የሸኽ ሙሐመድ ሶብዩ ዚከር “ዐለይከ ረበና ቢሁስኒል ኺታሚ …” አሁን ድረስ አብሮን አለ፡፡ ከአሱር ሶላት በኋላ የነበሩት የሼኽ ሙሐመድ ሐሰን ፈድሉ ትምህርቶችም የማይዘነጉ ናቸው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሁሉንም ቀናት ዒድ እንዲመስሉ ያደርግ የነበረው የረመዳን ወር ተጠናቆ የዒድ ዋዜማ ይመጣል፡፡ ከዋዜማው ቀደም ብሎ ለበዓሉ የሚደረጉ ዝግጅቶችም አሁንም ድረስ ይታወሱኛል፡፡
የዒድ አል-ፈጥር ዕለት
በዓሉ በዋዜማው የሚኖረው ድምቀት ከበዓሉ ዕለት አይተናነስም ማለቴን እንዳትዘነጉ፡፡ የበጉ፣ የዶሮው ጩኸት በተለይም እናታችን ማድቤት ገብታ በገበር ምጣድ በኮባ የምትደፋው የድፎ ዳቦ ሽታ ከአይረሴዎቹ ናቸው፡፡ ከቀናት በፊት ቀደም ብሎ ቤትን ማስዋብ፤ ለመዋብ አዳዲስ ልብስና ጫማ መግዛትም ከዋናዎቹ ዝግጅቶች ተርታ ይመደባሉ፡፡
በተለይም የቤታችንን ግድግዳ በኬንያ ወረቀት እና የቤታችንን ወለል በፕላስቲክ ምንጣፍ ለማስዋብ የምንደክመው ልዩ ድባብ ነበረው፡፡ ልብስ እና ጫማ ከወላጆቻችን ጋር መርካቶና ዳርማር (የዛሬው አንበሳ ጫማ ሱቆች) ሄደን የምንገዛው ነገር ፈፅሞ አይረሳኝም፡፡ አቤት ልብሱ ተገዝቶ በዓሉ ደርሶ እስኪለበስ ድረስ ያለው ጉጉት፡፡ ሌሊቱ እኮ ያለ ዕንቅልፍ ይነጋ ነበር፡፡
ከዚያም ለሱብሂ ሶላት ጠዋት 11፡00 ሰዓት በተነሳንበት ለበዓሉ ማብሰሪያ ከእንጦጦ ይተኮስ የነበረው መድፍም ሌላው ትዝታችን ነው፡፡ በተለይ ምን ያህል እንደተተኮሰ የምንቆጥረውም ነገር እንደዛው፡፡ በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው በዓል ከደረሰ በኋላ በጠዋት በየተራ ገላችንን ታጥበን አዲሱን ልሳችን እንለብሳለን፡፡ በዚህ መሃል እናቶች ቤቱን ያስውባሉ፤ የገንፎዋ ነገርማ አሁን ድረስ ጣዕሟ ውስጥ አለ፡፡ ማለዳ እሷ ሳትበላ ንቅንቅ የለማ፡፡
ከዚያ በኋላ ነው ከቤተሰብ እና ከአካባቢው ሙስሊሞች ጋር በመሆን የበዓሉን ዋና ተግባር “የዒድ ሶላት ለመስገድ እና ኹጥባ ለማዳመጥ” ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ተክቢራ በማለት አንድ ላይ ተሰብስበን የምንተመው፡፡ አቤት ድባቡ ማማሩ፡፡ ሶላቱ ተጠናቅቆ ኹጥባ አዳምጠን ከጨረሰን በኋላ እንደ አመጣጣችን በቡድን በቡድን ሆነን መንዙማ ከሚሉ ወጣቶች ጋር ወደየቤታችን እንመለሳለን፡፡
ቤት ከደረስን በኋላ ቡና ተፈልቶ፣ ቄጠማ ተጎዝጉዞና ድፎ ዳቦ ቀርቦ ጎረቤቶቻችንን ጥሩ እንባላለን፡፡ ልዩ የሆነው የቡና ስርዓት ከወትሮ በተለየ መልክ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በስተመጨረሻም “የዓለም የሲሳይ ቤት ይሁን ዓመት ዓመት ያድርሰን” በሚል ተመርቆ ወደ ተከታዩ ምዕራፍ በመሸጋገር ዘመዶችን ተቀብሎ በማስተናገድና ቤት ያፈራውን አብሮ በመቃመስ እና በየመሀሉ በሚመጡ ጨዋታዎች በጋራ ቀኑን በድምቀት እናሳልፋለን፡፡ በዚህ መልኩ ነበር የልጅነት እና የአፍላ ወጣትነት ዕድሜያችን የዒድ አል-ፈጥር በዓል ያሳለፍነው፡፡
ወደ ሊቢያ
ይህኛው ምዕራፍ ተጠናቅቆ ደግሞ ፍፁም ሌላ ወደ ሆነው የህይወት ተሞክሮ የገባነው እኔን ጨምሮ 12 ጓደኞቼ በሃያዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ሳለን የትምህርት ዕድል በማግኘት በሙዓመር ጋዳፊ የአስተዳደር ዘመን ወደ ሊቢያ አመራን፡፡ በውጭ ሀገር ያለው የበዓል አከባበር ተሞክሮ ደግሞ ከላይ በሀገር ውስጥ ካነሳነው የአከባበር ሂደት በእጅጉ ይለያል፡፡
አስታውሳለሁ የትምህርት ዕድሉን አግኝተን ወደ ሊቢያ ባመራን ጊዜ እዚያ የደረስነው በመጀመሪያው የረመዳን ሌሊት ነበር፡፡ እናም ያገኘነውን በመቅመስ ሱሁራችንን አሰርን፡፡ ከሀገሬው ነዋሪዎች እና ነባር ተማሪዎች ጋር የመጀመሪያ የረመዳን ቀን ፆም እኩል ያዝን፡፡
ሙቀቱና የቀኑ ርዝመት ከኛ ሀገር ጋር በጣም ይለያያል፡፡ ሌሊት ሱብሂ 10፡00 ሰዓት አዛን ብሎ ምሽት 2፡00 መግሪብ አዛን ይላል፡፡ ይህም ማለት በፆም የምናሳልፈው ወቅት ከ17 ሰዓታት በላይ ነበር፡፡ ልጅነትና ለአዲስ ነገርም ጉጉት ስለነበረን እምብዛም አልከበደንም፡፡ ትልቁ ተግዳሮት የነበረው ያ ከቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ዘመድ ጋር የለመድነው የረመዳን እና የዒድ ድባብን መናፈቃችን ነበር፡፡
ሾርባ ቢናፍቀንም ለእኛ አዲስ የሆነውን የሀገሪቱን ባህል ለመላመድ ግዜ አልፈጀብንም፡፡ ጥሩ ዘመን ነበርና ህዝቦቿ የባህር ሙሽራ በሚሏት ትሪፖሊ ከተማ ጥሩ ጊዜ አሳለፍን፡፡
ከእኛ ቀደም ብለው ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ጊዜ በኋላ ስለሆነ ኢትዮጵያዊያንን ያዩት በናፍቆት ነበር ያስተናገዱን፡፡ በተባረከው የረመዳን ወር የሊቢያን ምድር እና ህዝብ ከተዋወቅን በኋላ የፆሙ ወር ሲጠናቀቅ ባጋጠመን ልዩ ገጠመኝ በወፍ በረር ያስቃኘኋችሁን የዒድ አል-ፈጥር በዓል አከባበር ትዝታዎች ልቋጭ፡፡
ዒድ አል-ፈጥር በሊቢያ
ቀደም ብዬ እንዳነሳሁላችሁ ከእኛ ቀድመው በዩኒቨርሲቲው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በእኛ ወደ እነሱ መቀላቀል በጣም ደስተኞች ነበሩ፡፡ በወሬ ወሬ የዘንድሮውን ዒድ እንዴት ለየት ባለና የሀገር ቃና ባለው መልኩ ማሳለፍ እንዳለብን፣ እንጀራ እና ዶሮ ወጥ እንዴት ማዘጋጀት እንደምንችል ሀሳብ ተለዋወጥን፡፡
ዩኒቨርስቲው በውስጡ አስፈላጊ የተባሉ ተቋማትን አካቷል፡፡ በተለይም ለእኛ በዚያ ሰዓት አስፈላጊ የነበረው ለእንጀራ መጋገሪያ የሚሆን ዱቄት ማግኘት ነበር፡፡ በተቋሙ ከነበረው ትልቅ የተማሪዎች ዳቦ መጋገሪያ በምሽት ሄደን ለዳቦ ከሚያቦኩት ሊጥ እንዲሰጡን ጠየቅን፣ “ደግሞ ጠይቃችሁን ነው?” በሚያሰኝ መልኩ በደንብ አድርገው ሰጡን፡፡ ከዚያም ከተቋሙ ሱፐር ማርኬት እርሾ እና ዶሮ ገዝተን ወደ ዶርማችን ተመለስን፡፡ አስፈላጊ ግብአቶች ከተሟሉ በኋላ የሁሉም ተነሳሽነት ጨመረ፡፡ ሰፋ ባለ ባልዲ ሊጡ በደምብ እርሾ ተደርጎበት ተቦካ፡፡ በጠዋት ተነስተን እንደምንጋግረው ተነጋግረን ወደ መኝታ ሄድን፡፡ ጠዋት ለሱብሂ በተነሳንበት ወደ መጠባበሻ ክፍል ስንገባ ያየነው ነገር ሁላችንንም አሳቀን፡፡ የሙያ ጉድለታችን በሀሳብ ወደ ሀገር ቤት መልሶን የእናቶቻችንና እህቶቻችንን ልፋትና ጠንቃቃነት አስታወሰን፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው ያቦካነው ሊጥ እርሾው ከአቅም በላይ ሆኖበት በመገንፈሉ ወለሉ ላይ ቀድሞ እራሱን ጋግሮ አገኘነው፡፡ ይህን አጋጣሚ መቼም አንረሳውም፡፡ የሆነው ሆኖ ከመፍሰስ የቀረውን ሊጥ በመጠቀም ሰፋ ባለ የእንቁላል መጥበሻ ካሰብነው በላይ በብዛት ጋገርን፡፡ ዶሮዋን ከመካከላችን የተሻለ ዕውቀት ያለው ሰው ስለነበር አላህ ይዘንላትና አክስቴ በቋጠረችልኝ በቂቤ የታሸ በርበሬ አጣፍጠን ሰራን፡፡
በበዓሉ በጣም ደስ ከሚለውና ከማይረሳው ትዝታችን የእኛ ኢትዮጵያውያን ትስስር ብቻ የታየበት ሳይሆን እንደዛ ተጨንቀን በሰራነው ወጥና እንጀራ አፍሪካውያን ተማሪዎች በተለይም ከሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ የመጡ ተማሪዎች ዘንድ የነበረው የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ እንዲያውም እነዚህ ህዝቦች ለኢትዮጵያ ያላቸው ክብርና ቦታ ላቅ ያለ መሆኑን በተጨባጭ ያየንበት የህይወት አጋጣሚም ሆኖ አልፏል፡፡
ስለ ሊቢያ እና ህዝቧ ደግነት በተለይም በመሪዋ ጋዳፊ ለእኛ ዓይነት የውጭ ሀገር ተማሪዎች ይደረግ የነበረው እንክብካቤ እና በተለይ የዒድ አል-አድሃ በዓል በመጣ ቁጥር ይሰጠን ስለነበረው የበግ ስጦታና ሌሎችም የቀሩ ትዝታዎች በሰላም ያድርሰን እና ከሁለት ወር በኋላ የሐጅ ስርዓትን መጠናቀቅ ተከትሎ በሚመጣው የዒድ አል-አድሃ በዓል ዳግም በብዕሬ እስከምተርክላችሁ ቸር ያቆየን እላለሁ፡፡ መልካም በዓል፡፡ ኢድ-ሙባረክ፡፡
በአሚር በድሩ