አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር የሶላት ሥነ ሥርዓት በድምቀት ተከብሮ ተጠናቅቋል አለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፡፡
መምሪያው እንዳስታወቀው÷ የሶላት ሥነ ሥርዓቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት እቅድ በማውጣት ወደ ተግባር መግባታቸውን አስታውሷል፡፡
መምሪያው ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጋር በትብብር በመስራቱ ስኬታማ የዒድ ሶላት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት እንዲካሄድ ማስቻሉን አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረገው የዔድ ሶላት በስኬት እንዲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ተገቢውን ትብብር ማድረጋቸውን የገለጸው ፖሊስ÷ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የከተማውን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚከናወኑ ልዩ ልዩ ተግባራት ላይ ህብረተሰቡ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አስተላልፏል።