አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ከ32 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ተሰብስቧል አለ የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ።
በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀብታሙ ሁነኛው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ 33 ሺህ 330 ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት 32 ሺህ 642 ቶን የማር ምርት ማግኘት መቻሉን ገልጸው÷ ምርቱን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በስፋት እንዲመረት ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ የንብ ማነብ ባለሙያ አለምነሽ ዘውዱ በበኩላቸው÷ በከተማዋ ባለፉት ስምንት ወራት 354 ቶን የማር ምርት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሙሉጌታ ደሴ