የሀገር ውስጥ ዜና

‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ የባለራዕይ መሪ የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ምስክር ነው – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

By Adimasu Aragawu

March 22, 2026

‎አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ማህበረሰብን ለማበልጸግና ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የባለራዕይ መሪ የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ምስክር ነው አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት።

ጽሕፈት ቤቱ ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ሁሉን አቀፍ ምድራዊ ገነት በሚል ባወጣው መረጃ እንደገለጸው÷ ‎በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ’ገበታ ለትውልድ’ ውጥን አካል የሆነው ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ማህበረሰብን ለማበልጸግና ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የባለራዕይ መሪ የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ምስክር ነው። ‎ ‎ሎጅው በተለያዩ የፍራፍሬ እና የደን ዛፎች በለመለመ 78 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን ገልጿል።

ተፈጥሯዊ የ”ሰማያዊ ዓይን” ፍልውሃ መዋኛ፣ ሁለት ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቆች እና 3 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግር ጉዞ (ሀይኪንግ) ምቹ መንገድ ያካተተ መሆኑንም አብራርቷል።

‎ሎጅው የማረፊያ ክፍሎቹንም በተመለከተ፦ የግል መዋኛ ገንዳ ያላቸው ሁለት ፕሬዚዳንታዊ ቪላዎች፣ 12 እርስ በእርስ የተያያዙ የመኝታ ክፍሎች እና 16 ባለአንድ መኝታ ቤቶችን መያዙንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

በተጨማሪም ዘመናዊ የምግብ አዳራሾች፣ የእንግዳ መቀበያ ህንፃ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የቢሮ ክፍሎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና ሁለት ሄሊኮፕተሮችን በአንድ ጊዜ ማሳረፍ የሚችል ስፍራ (ሄሊፓድ) ያካተቱ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታልም ብሏል። ‎ ‎ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ከቱሪስት መዳረሻነቱ ባለፈ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን በመሳብ ታላላቅ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ተደማሪ ዐቅም እንደሆነም አብራርቷል።

‎በመስተንግዶ እና በአገልግሎት ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአካባቢው ኢኮኖሚ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ሲሆን÷ ፕሮጀክቱ በጠንካራ አመራር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻን የማቅረብ የገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር ርዕይን ሰንቆ ቀጣይነት ላለው ቀጣናዊ ዕድገት እንደ ወሳኝ ሞተር ሆኖ ያገለግላልም ነው ያለው ጽሕፈት ቤቱ በመረጃው።