የሀገር ውስጥ ዜና

ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ያዘጋጀውን ማኒፌስቶ ይፋ አደረገ

By Adimasu Aragawu

March 24, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያዘጋጀውን ማኒፌስቶ ባዘሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ፓርቲው በዓድዋ ድል መታሰቢያ ባዘጋጀው መድረክ ማኒፌስቶውን ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ 7ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል።

በ2011 ዓ.ም የተመሰረተው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሀገሪቱ በሐሳብ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ምህዳር ለመገንባት የራሱን ዐሻራ ማበርከቱ ገልጿል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለኢላ አሊ እንዳሉት÷ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ጤናማ ፉክክር በማድረግ በምርጫው ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራ ይገኛል።

ፓርቲው 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ የሚመራበትን ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ነእፓ በ2013 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ በመሳተፍ ልምድ መቅሰሙን የገለጹት ኃላፊው÷ ከዚህ በመነሳት በዘንድሮ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሚዛናዊና ምክንያታዊ የፖለቲካ ዕይታን እከተላለሁ ያለው ነእፓ÷ “ፓርቲ እጩ መንግሥት ነው” ነው በሚል አቋም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መስክ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል።

በመድረኩ ፓርቲው ለእጩዎቹና ለሚዲያ ባለሙያዎች ማኒፌስቶን በዝርዝር ያብራራ ሲሆን÷ የምርጫ ምልክቱም ብዕር መሆኑን አስረድቷል።

በምንተስኖት ሙሉጌታ