አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም ሀገራት የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ከመፍሄዎቹ መካከል አሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የመጠቀም አማራጭን ማሳደግ አንዱ ነው።
በመሆኑም በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረው ጦርነት ወሳኝ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥ አገልግሎት ማስተጓጎሉ በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ አስከትሏል።
በዚህም የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በመሻገሩ፤ ሀገራት የነዳጅ እጥረትን ለመቋቋም የተለያዩ ውሳኔዎችን ከማስተላለፍ በተጨማሪ ታዳሽ ሀይልን እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ ይገኛል፡፡
የነዳጅ ዋጋ በ36 በመቶ ጭማሪ ያሳየባት አውስትራሊያ፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት እያስተዋወቀች መሆኗ ተገልጿል።
ይህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ አዲስ ክብረ ወሰን ሲያስመዘገብ፤ ከአጠቃላይ የቀላል መኪናዎች ሽያጭ የኤሌክትሪክ መኪና ድርሻ 12 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱ ተነግሯል።
የቤንዚን ዋጋ 18 በመቶ ጭማሪ ያሳየባት ጃፓን ነዳጅ ለመቆጠብ ካወጣቻቸው ህጎች ባሻገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በብዛት ገበያ ላይ እንዲውሉ አድርጋለች።
ፈረንሳይ፣ ሲንጋፖር፣ ፊሊፒንስ፣ ስሪላንካ፣ ታይዋን፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ተመሳሳይ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን ወደ መጠቀም ፊታቸውን እያዞሩ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።
በዓለም ቁጥር አንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች የሆነችው ቻይና አሁን ከተፈጠረው የኤሌክትሪክ ተሸካርካሪ ፍላጎት አንፃር አዲስ የኢኮኖሚ እድል ሊፈጠርላት ይችላል መባሉን የዘገበው ደግሞ ሲጂቲኤን ነው።
በሚኪያስ አየለ