አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተሞች በመደመር መንግሥት እንደ ዋነኛ ማህበራዊ መሰረት ተደርገው ይወሰዳሉ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመት እና የኮሪደር ልማት በሚል መሪ ሐሳብ ከቃና ቲቪ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም የቀድሞ መንግሥታት ከተማን እንደ ስጋት፤ ነዋሪን ደግሞ እንደ ወላዋይ የማየት ዝንባሌ እንደነበራቸው አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱ የከተማን ነዋሪ የፖለቲካ እና የማህበራዊ መሰረት ከማድረግ ይልቅ የማግለል ልምምድ መታየቱ ትክክል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ከተማ ውስጥ በርካታ ሃብት መኖሩን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለአብነትም አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ግማሽ ያህል ዓመታዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) እንደምትሸፍን ጠቅሰዋል፡፡
ከተማ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋና እምነት ያላቸው ዜጎች ተስማምተው የሚኖሩበት በመሆኑ የአብሮነት ላቦራቶሪ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
የአንድ ሀገር ሥልጣኔ እና እድገት የሚለካው በከተሞች ነው፤ ስለሆነም ከተማ የሥልጣኔ መስተዋት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከተማን የብልጽግና ሞተር አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለከተማ ለውጥም ነዋሪዎች መሰረት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የከተማ ነዋሪዎችን ያለአግባብ በመፈረጅ ማግለል የሀገርን እድገት ለማረጋገጥ እንደማያስችል ነው ያስገነዘቡት፡፡
ከተሞች የውበት መታያ፣ የሀገር መኳያ፣ የዘመናዊነት መፈብረኪያ እና የቅልጥፍና መገለጫ እንደሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከተሞች ምርትና ፈጠራ የሚገኝባቸው በመሆኑ የሀገር እጅና አዕምሮ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሀገርን እድገት ለማሳለጥ ያላቸው ሚናም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ የሚገኙ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ብዙ አይነት ማሕበረሰብ በውስጣቸው የያዙና በርካታ ፈጠራዎች ያሉባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በመደመር መንግሥት ከተሞች እንደ ዋነኛ ማህበራዊ መሰረት ተደርገው እንደሚወሰዱ እና ከተሜነት ደግሞ እያደገ የሚመጣ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች ላይ እየተከናወነ በሚገኘው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ