አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በአፍሪካ የከተሜነት አኗኗር ዝመና ውስጥ ጉልህ አሻራ እያኖረች ነው አሉ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በዘላቂ የከተማ ልማትና ኢንቨስትመንት ያላቸውን አጋርነት ለማሳደግ ያለመው የመጀመሪያው የኢትዮ-ጣሊያን የኮንስትራክሽን፣ መሠረተ ልማትና የከተማ መልሶ ግንባታ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ የልማት ትብብር በከተማ መሠረተ ልማትና መልሶ ግንባታ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
አዲስ አበባ በአፍሪካ የከተሜነት አኗኗር ዝመና ውስጥ ጉልህ አሻራ እያኖረች ነው ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፥ የተረጋጋ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብር እንዲፈጠር ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የቀጣናው ሀገራት በልማትና በጸጥታ ሁኔታ ተባብረው እንዲሰሩ ፍላጎቷ ነው ብለዋል።
በዚህም ጣሊያን ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር፣ ለከተማ ልማትና መልሶ ግንባታ እንዲሁም ለኃይል መሠረተ ልማት እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
አዲስ አበባ በከፍተኛ የልማት ጉዞ ላይ ትገኛለች ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዚህ ረገድ ጣሊያን ያላትን የመሠረተ ልማትና የከተማ ኑሮ ማሻሻል ልምድ እንደምታካፍል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ምክትል ኃላፊ ማርያ ትሪፖዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲቀጥልና ቀጣናዊ የመሠረተ ልማት ትስስርን ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት።
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሰም ፋብሪዚ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አዲስ አበባ አሁን ላይ በዓለማችን በአስደናቂ እድገት ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ ናት፡፡
በኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ውስጥ በርካታ የጣሊያን ድርጅቶች አሻራቸውን እያሳረፉ እንደሚገኙ ገልጸው፥ በቀጣይም በከተማ መሠረተ ልማት ዝመና እንዲሁም በሀገር አቀፍ የልማት ተግባራት ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በመሠረተ ልማት ማስፋፋትና በሜጋ ፕሮጀክቶች ዘርፍ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው በፎረሙ ላይ ተነስቷል።
በአሸብር ካሳሁን