የሀገር ውስጥ ዜና

የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብሱን ሊቀይር ነው

By Tibebu Kebede

August 25, 2020

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብሱን ሊቀይር መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ገለፁ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫን አስመልክቶ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የነበረው ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ እንደሚቀየርና ጉዳዩን አስመልክቶ በመጪው ቅዳሜ ሰፊ ማብራሪያ በኮሚሽኑ እንደሚሰጥ በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

ለደንብ ልብሱ መቀየር አሁን ያለው የደንብ ልብስ በቀላሉ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ በስነ ምግባር ችግር የተባበሩ ፖሊሶች ልብሱን ለብሰው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

በዚህም የደንብ ልብሱን በመልበስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና ዝርፊያዎች መበራከታቸውን ነው ያስታወቁት።

በሌላ በኩል በ2013 ዓ.ም አዳዲስ የፖሊስ ዘርፎች በሙከራ ደረጃ ወደ ሥራ ሊገቡ እንደሆነ ኮሚሽነር እንዳሻው አያይዘው ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲ፣ የቱሪዝምና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፖሊስ በሚሉ ዘርፎች ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሙከራው የሚገኙ ልምዶችን በመውሰድ የፖሊስ ዘርፎቹ ወደፊት በዘላቂነት ሊሰራባቸው የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር መግለፃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።