አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም ዘርፍ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠሩ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመት እና የኮሪደር ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ ከቃና ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው ይህንን ያሉት።
ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲያመርቱ ከዚህ ቀደም የነበረው አጠቃላይ የቢዝነስ አሰራር አመቺ እንዳልነበረ ጠቅሰው÷ አሁን ላይ እየተሻሻለ የሚታዩ ለውጦች እየተመዘገቡበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢንዱስትሪ ዘርፍ የወጪ ንግድ ገቢ ከ250 ሚሊየን አያልፍም ነበር በማለት ገልጸው÷ አሁን ላይ ኢንዱስትሪዎች ከወጪ ንግድ ገቢ እያስገኙ እንደሆነና ይህም በዋዛ የመጣ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
አምስት የሶላር ኃይል ወደ ስራ ገብተው ግማሾቹ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በዚህም ከሶላር ብቻ በሚቀጥለው ዓመት ወደ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ እናገኛለን ብለዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣናዎች መገንባታቸውን አንስተው÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች ሌላ አዲስ ሳይጨመር በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ አሁን ያለው ምርታማነት እጥፍ እንደሚሆን አስረድተዋል።
በሶስና አለማየሁ