አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ።
4ኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም የመክፈቻ መርሐ ግብር “ለቢዝነስ ስራ ዝግጁ የሆነች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አቶ አሕመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ፎረሙ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የንግድ ማህበረሰብ ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግና በግሉ ዘርፍ የሚመራ የልማት ጉዞን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
መንግስት የግል ዘርፉ በኢንቨስትመንት እና በስራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዲያበረክት ክፍት የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ ሪፎርሞችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑ የኢኮኖሚ ለውጦች በመንግስት እና በግል ዘርፍ ጠንካራ አጋርነት ላይ የተገነባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፊስካል ሪፎርም ይበልጥ ግልጽ እና ሊገመት የሚችል የኢንቨስትመንት ምህዳር እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የታክስ አስተዳደሩ ዲጂታል መሆኑን ገልጸው÷ በስትራቴጂካዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለውና ቀልጣፋ ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ የሚያስችል አዲስ በአፈጻጸም ላይ የተመሰረተ የታክስና የወጪ አስተዳደር ስርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በቋሚነት እየጨመረና በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ያለው ዓለም አቀፍ ፍላጎት እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል አንስተው÷ ለምስራቅ አፍሪካና ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማዕከል እየሆነች መምጣቷን አመልክተዋል፡፡
በለይኩን ዓለም