የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በመመራት ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እየገነባች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Adimasu Aragawu

March 26, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በመመራት ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እየገነባች ነው አሉ፡፡

4ኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም የመክፈቻ መርሐ ግብር “ለቢዝነስ ስራ ዝግጁ የሆነች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተተገበረው የሪፎርም ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተመራች ተወዳዳሪ፣ ተገማችና ምቹ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እየገነባች ነው ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል የሆኑት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለውድድር ክፍት ማድረግ እና በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሪ መተግበር በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ከባቢ ምቹ እያደረገው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት ከባቢ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት በተሟላ መልኩ ምቹ መሆን እንዳለበት ገልጸው÷ የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ሁኔታ ትርጉም ባለው መልክ ማሻሻል እስካልቻለ ድረስ በተገኙ ስኬቶች መዘናጋት እንደማይገባ አብራርተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ፎረሙ የፌዴሬሽን ምክር አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

በለይኩን ዓለም