አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ህግ የሰበር ሰሚ ዳኞችን ፊርማ አመሳስሎ በመፈረምና ሀሰተኛ ውሳኔ በማዘጋጀት ወንጀል በተጠረጠረው የህግ ባለሙያ ላይ ክስ መስርቷል።
ዐቃቢ ህጉ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት የህግ ባለሙያ (ጠበቃ) በሆነው ዮናስ ደርብ አባተ እና አስናቀች ሀጎስ ገብረህይወት በተባለች ግለሰብ ላይ ነው ክሱን የመሰረተው።
ዐቃቢ ህግ እነዚህ ተጠሪጣሪዎች ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር (1) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር (3) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ክስ አቅርቧል።
በዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው÷ ተከሳሾቹ የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሳቸው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሁለተኛ ተከሳሽ ከሌላ ግለሰብ ጋር ለነበራቸው የ84 ሚሊየን ብር የቡና እርሻ ክርክር ጉዳዩ በጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ንብረቱን ሁለተኛ ተከሳሽ ለተከራካሪ ግለሰብ እንድታስረክብ የሚል ውሳኔ ተወስኖ ነበር።
ይሁንና በዚህ መልኩ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ በመቀየር የህግ ባለሙያ (ጠበቃ) የሆነው አንደኛ ተጠርጣሪ በመስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም በሰባት ዳኛ የተፈረመበት የሚመስል ሀሰተኛ ውሳኔ ማለትም ክርክር የተነሳበትን የቡና እርሻ ተከራካሪ ግለሰቡ ለሁለተኛ ተከሳሽ አስረክበው የመጨረሻ ውሳኔ እንዲጠባበቁ የሚል እና የስር ፍ/ቤቶችም ይህንን ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ የሚል ከጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደተሰጠ በማስመሰል የመዝገብ ቁጥር በመጥቀስ ሀሰተኛ የፍርድ ቤት ውሳኔ ለሁለተኛ ተከሳሽ መስጠቱን ዐቃቢ ህግ በክሱ ዝርዝር ላይ አቅርቧል።
በዚህ መልኩ ሁለተኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ ውሳኔውን ከአንደኛ ተከሳሽ ከተቀበለች በኋላ የመዝገብ ቁጥር የተጠቀሰበት አቤቱታ በሌላ ግለሰብ እንዲዘጋጅ በማድረግ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐብሔር ከውል ውጭና ልዩ ልዩ ባለ ሶስት ዳኞች ችሎት እንዲሁም ለንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ መሆኑን ዐቃቢ ህግ በክሱ ዝርዝር ላይ ጠቅሷል።
በመጨረሻም ሁለተኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ ውሳኔዎች አባሪ የተደረጉ መሆኑን የሚገልጽ ሀሰተኛ መሸኛ ደብዳቤን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በማቅረብ የተገለገለች መሆኗንና በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ዐቃቢ ህጉ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህ መልኩ በተከሳሾች ላይ የቀረበው የክስ መዝገብ የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 6ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት መዝገቡን ለመጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ