አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር እያደረጉት የሚገኘው ጦርነት ወደ ዓለም አቀፍ ቀውስ ተሸጋግሯል።
በፈረንጆቹ ባሳለፍነው የካቲት 28 ቀን በአሜሪካ እና እስራኤል የሚሳኤል ጥምር ጥቃት የ86 ዓመቱ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊኻሚኒ መገደላቸውን ተከትሎ ግጭቱ ወደ ቀጣናዊ ጦርነት መስፋፋቱ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካና እስራኤል ኃይሎች በ12 ሰዓታት ውስጥ ብቻ የኢራን ከፍተኛ አመራሮችን፣ የኒውክሌር ጣቢያዎችን እና የሚሳኤል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ወደ 900 የሚጠጉ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
እስራኤል እስካሁን ድረስ በኢራን ላይ ከ15 ሺህ በላይ የሚሆን የተለያዩ ጥቃቶችን መፈጸሟን የገለጸች ሲሆን÷ በዚህም በቴህራን የክሩዝ ሚሳኤል ማምረቻና የኢስፋሃን የውስጥ ለውስጥ የውሃ ምርምር ተቋምን ጨምሮ ቁልፍ የኢንዱስትሪ ኢላማዎችን ማውደሟን አስታውቃለች።
በተመሳሳይ አሜሪካ 17 የሚሆኑ የኢራን የጦር መርከቦችን ማስጠሟን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ቁልፍ የሚሳኤል ማምረቻ ቦታዎችን፣ የባህር ኃይል ንብረቶችን፣ የወታደራዊ ማዘዣ ተቋማትን፣ የነዳጅ ማከማቻዎች እና የነዳጅ ማጣሪያዎችን እንዲሁም ወሳኝ የኃይል ማመንጫ ተቋማት ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች፡፡
ቴህራን በአጸፋዊ ርምጃዋ እስራኤልን ጨምሮ በቀጣናው በሚገኙ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ላይ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች፣ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎችና የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ላይ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃቶችን አድርሳለች፡፡
እንዲሁም በዓለም ወሳኝ የሆነውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በመዝጋት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ትገኛለች።
አንደኛ ወሩን ለመድፈን የቀናት ዕድሜ ብቻ የሚቀሩት ጦርነቱ አሁንም ይበልጥ እየተባባሰ ሲሆን ÷ ከሁሉም ወገን የሚፈጸመው ጥቃት እንደቀጠለ ነው፡፡
በአሜሪካ በኩል በጦርነቱ እስካሁን 13 ወታደሮች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ÷ ወደ 290 የሚሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በመሠረተ ልማቶች ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተመላክቷል።
የአሜሪካ ንብረት የሆኑ መሠረት ልማቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች 17 የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በደረሰ ጉዳት እስከ 800 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ደርሷል፤ 12 ዘመናዊ የራዳር ሥርዓቶች እና የሳተላይት ተርሚናሎችም ተመትተዋል።
ከእስራኤል በኩል 22 ሲቪል እና 4 ወታደሮች በአጠቃላይ 26 ሰዎች ሲገደሉ ÷ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተጠቁሟል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች የምትገኘው ኢራን በነዳጅ ማጣሪያ መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ጉዳት ያስተናገደች ሲሆን ÷ በቴህራን ከሚቃጠሉ የነዳጅ ማከማቻዎች የሚወጣው መርዛማ ጭስ አሲዳማ ዝናብ እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል።
ከዚህ ባለፈም በጦርነቱ በቴህራን እስካሁን በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሕልፈት ሲዳረጉ÷ ከ85 ሺህ በላይ የሲቪል ቦታዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡
በእነዚህ ጥቃቶችም ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደርሰበቸው እና ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን÷ በጥቃቱ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸው እና ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡
የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ የተፈጠረ ሲሆን÷ ለአብነትም የዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት በቀን በ8 ሚሊየን በርሜል እንዲቀንስና የነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል ወደ 120 ዶላር እንዲጠጋ አድርጓል።
በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ጦርነት የኒውክሌር መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተፈጽሙ ነው ፤ በዚህም ከፍተኛ ውድመት እየደረሰ ይገኛል፡፡
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጉዳት አስከፊ የራዲዮአክቲቭ ብክለት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር እያደረጉት የሚገኘው ጦርነት የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ፤ በቢሊየን ዶላር የሚገመት ንብረት እያወደመ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የቢቢሲና ሬውተርስ መረጃ ያመላክታል፡፡
በዮናስ ጌትነት