የሀገር ውስጥ ዜና

ሹዋሊድ በዓል የሐረሪ ሕዝብ ካሉት በርካታ ድንቅ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው – የቱሪዝም ሚኒስቴር

By Yonas Getnet

March 26, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስቴር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለተመዘገበው የሹዋሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ለዘመናት በኩራት ለዘለቀውና በዓለም ቅርስነት ለተመዘገበው ለዘንድሮው የሹዋሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ያለው ሚኒስቴሩ÷ በዓሉ የሐረሪ ሕዝብ ካሉት በርካታ ድንቅ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው ብሏል።

ከረመዳን ጾም መጠናቀቅ በኋላ የሚከበር የደስታ፣ የፍቅር እና የማሕበራዊ ትስስር መገለጫ እንደሆነ በመግለጽ÷ በዓሉ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አቅም ይዞ የመጣ ብርቅዬ ሀብት እንደሆነ አንስቷል።

በዓሉን ስናከብር ኢትዮጵያ ያላትን ጥንታዊ ሥልጣኔና ለዓለም ያበረከተችውን ድንቅ የባህል ሀብት በኩራት እያስታወስን ሊሆን ይገባልም ነው ያለው።

በታሪካዊቷ የሐረር ጀጎል ግንብ ውስጥ የሚከበረው ይህ ደማቅ በዓል፣ በባሕላዊ ጭፈራዎች፣ ውብ በሆኑ አልባሳትና የሐረሪ ሕዝብ የእንግዳ ተቀባይነት ሥነ ሥርዓቶች የታጀበ በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ቀልብ የመሳብ ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘውን የሹዋሊድ በዓል ለዓለም በማስተዋወቅ፣ ሐረርን ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም አመልክቷል።

ሹዋሊድን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ሁሉም ኃላፊነት እንዳለበት ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል።