የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ዘመናዊነት ጉልህ ሚናን ተጫውተዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By sosina alemayehu

March 26, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ለዘመናዊነት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ ይህን ያሉት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

በከተማ አስተዳደሩ አራተኛው አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በ20 ተቋማት እና 112 አገልግሎቶች ስራ መጀመሩ ተመላክቷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንደ ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰጡ 600 አገልግሎቶች 240 የሚሆኑት በዲጂታል የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

አገልግሎቶቹ ሕዝብን ለእንግልት በመዳረግ የቅሬታ ምንጭ ሆነው በመቆየታቸው ቅድሚያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ አገልግሎቶችም እስከ መጪው የበጀት ዓመት በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል እንዲገቡ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት።

በማዕከሉ የተገልጋዩ እርካታ 98 በመቶ መሟላቱ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋፋት የሚያነሳሳ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀናጀና የተናበበ በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በየትኛውም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሂደቱ ቅልጥፍናን የሚጨምር በመሆኑ ይበልጥ በማዘመን ሁሉም በቤቱ ሆኖ በተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎቶቹን የሚያገኝበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በታምራት ደለሊ