አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በካሜሩን ያውንዴ እየተካሄደ ባለው የዓለም ንግድ ድርጅት ሚኒስትሮች ጉባኤ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ያደረገችውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀዋል።
በካሜሩን ያውንዴ ዛሬ በተጀመረው 14ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት ሚኒስትሮች ጉባኤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ያደረገችውን ከፍተኛ ጥረት በማድነቅ 166ቱ የድርጅቱ አባል ሀገራት ዕውቅናና አድናቆት እንዲሰጧት ጉባኤውን በይፋ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የድርድር ቡድን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ያሳካው እመርታ ባለፉት 22 ዓመታት ካደረገችው እንቅስቃሴ እጅግ የላቀ መሆኑንም አመልክተዋል።
ይህም የመንግሥትን ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው÷ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የአባልነት ድርድሯን እንድታጠናቅቅ ድጋፍ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።