አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ በደረሰ ጥቆማ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ46 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ተይዟል አለ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፡፡ ሕገ ወጥ ነዳጁ የፌደራል የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባደረገው ኦፕሬሽን ነው ከእነ አዘዋዋሪዎቹ የተያዘው፡፡
በዚህ መሰረትም በሸገር ከተማ አስተዳደር ቱሉ ዲምቱ ወረዳ ከሚገኝ የነዳጅ ማደያ ታንከር 46 ሺህ ሊትር ቤንዚን ወደ ተሽከርካሪ በመቅዳት ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ተሽከርካሪ እጅ ከፍንጅ ተይዟል። በተመሳሳይ በሕገ ወጥ መንገድ የነዳጅ ታንከር በማስገጠም እና እንቁላል አከፋፋይ በመምሰል ነዳጅ ሲያከፋፍል የነበረ ተጠርጣሪ ከአራት ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቅሷል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ግቢ ውስጥም እያንዳንዳቸው 200 ሊትር ነዳጅ የያዙ ከ12 በላይ በርካታ በርሜሎች መገኘታቸው ተመላክቷል፡፡
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የሚገባን ነዳጅ በመደበቅና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ተቋማትን ሕብረተሰቡ እንዲያጋልጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወር ነዳጅ ሲመለከቱ በዜጎች መተግበሪያ፣ በሰው አልባ ስማርት ፖሊስ ስቴሽን፣ በ991 ነፃ የስልክ መስመርና ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡም ተጠይቋል፡፡