አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአርሶ አደር በሬ ገዝተው በሞባይል ባንክ ገንዘብ ያስተላለፉ አስመስለው የማታለል ወንጀል የፈጸሙት ሙህዲን ሙዘሚል እና ኑርሂማድ መካ በእስራት እና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የሸገር ከተማ አስተዳደር የሰንዳፋ በኪ ወረዳ ፍርድ ቤት ወስኗል።
የሰንዳፋ በኪ ወረዳ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 692 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ የማታለል ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾቹ ለራሳቸው ያልተገባ ሀብት ለማግኘት በሕዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም በሰንዳፋ የከብት ገበያ ከግል ተበዳይ አርሶ አደር ግርማ አብራር ወይፈን በሬ ለመግዛት ተስማምተዋል።
ነገር ግን ለበሬው ግዢ መፈጸሚያ በሚል በግለሰቡ የባንክ ሂሳብ ሁለተኛ ተከሳሽ በሞባይል ባንኪንግ 39 ሺህ ብር ያስተላለፈ አስመስለው ሞባይላቸው ላይ የተጻፈ ሀሰተኛ የመልክት ጽሁፍ ለአርሶ አደሩ በማሳየት በሬውን ይዘው መሰወራቸው በክሱ ተመላክቷል።
የግል ተበዳይ ወዲያው ገንዘቡን ለማውጣት ወደ ባንክ በሄደበት ወቅት ገንዘቡ አለመግባቱን ከባንክ በተሰጠው ማረጋገጫ መሰረት ጉዳዩን ለፖሊስ ያመለከተ ሲሆን የሰንዳፋ ፖሊስ መምሪያ በጥቆማው መነሻ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም ወንጀሉ በተፈጸመ ከአንድ ወር በኋላ ተከሳሾቹ በድጋሚ ወደ ሰንዳፋ የከብት ገበያ በመሄድ በሌላ አርሶ አደር ላይ ተመሳሳይ የማታለል ወንጀል ተግባር ሊፈጽሙ ሲንቀሳቀሱ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት ክደው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በችሎት አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆን መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት በቅጣት ማቅለያነት በመያዝ እያንዳንዳቸውን በ2 ዓመት ከ6 ወራት እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ